መመርመር : ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት እና መጽሐፍ-ቅዱስ ክፍል አንድ
ሰዶም እና ገሞራ (ዘፍ 19፡20-27) እንዲሁም የጊብዓ ሰዎች (መሳ 19፡22-27)
መግቢያ
‹ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እግዚአብሔርን መካድ፣ የተሰበረው በኃጢአትም መውደቅ ምክንያት የተፈጠረ ስህተተኛ ተፈጥሮ አንደሆነ፣ የተጠላ፣ አፀያፊ እና እንዲሁም ከሁሉ በላይ ኢሞራላዊ ኃጢአት እንደሆነ የምናምነው እንደ አለት የፀና የዘመናት እውነታችን ሆኖ ለብዙ ዘመን ሲነገረን ኖሯል ነው፡፡ ነገር ግን በ‹‹ነው›› ተቀብለን ‹‹ነው›› ካልን በውስጣችን ያለው መሰረት ሆነ እውነት የእኛ ሳይሆን የሰዎች መሆኑ እርግጥት ነው፡፡ የእ/ር ቃል የተፃፈው በመንፈስ ቅዱስ ነው ይህም ቃል የሰውን ልጅ ሁሉ የእ/ርን ፍቃድ የሚያስተምር ነው፡፡
የተወደዳችሁ ሁላችሁ ፍቅር በሆነው በአንዱ ጌታ የተፈቀራችሁ ናችሁ፡፡ አሁን ግን ሀዘኔ እና መከፋቴ በንፁህ እና አድሎ በሌለበት መንገድ የቃሉን እውነት ‹‹ዜጋነትን›› በተመለከተ በተፃፉት 7 ጥቅሶች ላይ ጥናት ለማድረግ አነሳስቶኛል፡፡ አንዴ አንድ ሰው ‹‹ስለልምምድህ ስትል የእ/ርን ቃል እውነት ትሽራለህ›› ብሎኝ ነበር እውነት ነው ልምዴ በልጦብኝ ቃሉን ኮንኛለው ስህተት ነው ስል ለራሴ የደገምኩባቸው ቀናቶች ነበሩ ይኮንነኝ ዘንድ ስልጣን የለውም ብዬ አውቃልሁ፡፡ነገር ግን ይሃ ራሴን በመጥላት እና ስህተተኝነቴን ውስጤን በገደለው ጊዜያት ያወራዋቸው የቃሉ እውነት እስኪገባኝ የተናገርኳቸው ናቸው የቃሉ እውነት እስኪገባኝ አዎ የተነገረኝ ‹‹ነው›› ለእኔም ‹‹ነው ሆኖ ከፈጣሪዬ ብቻ ሳይሆን ከራሴም ለይቶኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ‹‹ነ-ዌን›› የቃሉን ‹‹ነው›› ለማድረግ ቀርቢያለሁ የሰው ነው ነፍስን ያጠፋል የቃሉ ብርሃን ግን ሰላም ያደርጋል፡፡ ሰው በውስጡ ያለውን የእምነትን እሳቤ ያራሱ ይሁን የሌላው እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልገዋል፡፡አንዳንድ የሚሰሙን የምናውቃቸው ነገሮች የእኛ ይመስሉናል ነገ ግን የእኛ ያልሆኑ በሌሎች የተሰገሰጉ ሊሆን ይችላሉ ስለዚህ ስለምናውቀው ስለሚሰሙን ነገሮች የራሳችን ስለመሆናቸው ልናረጋግጥ
የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ስልት (Hermeneutics)
Hermeneutics ምንድነው? ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት ይህን መረዳት ያለብን ይመስለኛል ቃሉ እንደሚል "፤ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤" (2ኛ የጴጥ 1: 20) መጽሐፍ ቅዱስ ወጥ የሆነ የአፃፃፍ ስልት እንዳልሆነ ከማንበብ ብቻ መረዳት ምንችለው ነው፡፡ ስናነበው ታሪክ፣ግጥም፣መልዕክቶች፣የጥበብ ምክሮች፣ራዕይ/ ትንቢት፣ተምሳሌታዊ ገለፃ እና ሌሎች በርካታ ይዘት የተከተለ ነው፡፡ በዚህም እንደወረደ ለራሳችን መጠቀም እንደማንችል መረዳት ያስፈልጋል ታሪክ ቢያስተምረንም ልንተገብራቸው ግን ማንችላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው የመጽሐፍ አተረጓጎም ወይም ሄርሜኑቲክስ መጠቀም ያስፈለገን፡፡ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም እና አጠናን መርህ ወይ ሳይንስ/ጥበብ ልንለው እንችላለን፡፡ ስለዚህም
“Hermeneutics is the science of understanding and interpreting scripture”
ለዚህም ለዚህም ዐቃቤ-እምነቶች ፣ ስነ መለኮት አጥኚዎች ፣ ሆኑ ጸሐፍት አስተማሪዎች ቃሉ የሚለውን ትክክለኛ እና ፍሬ ነገር ላለመሳት የአፈታት መንገድ የሚጠቀሙት፡፡
ለምናነበው ለምናጠናው ክፍል የምንሰጠው አመለካከት ትክክለኛ ካልሆነ ቃል ክፍሉ ሊል ያልፈለገውን ብሏል ብለን ልንደመድም እንችላልን፡፡ ሰለ ሄርሜኑቲክስ ጠለቅ ያለ ነገር ማብራራት በራሱ ሌላ ለዥም መጽሐፍ ያሻዋል ነገር ግን ሁለት አይነት የአተረጓጎም ስልቶችን እና ሂደቶችን ላሳይና ወደ ሌላ ርዕስ እናልፋለን፡፡ነገር ግን ሁላችን ይበልጥ ልባችንን አነቃቅተን ለህይወታችን ግራ መጋባት የሆነውን ነገር እልባት ለመስጠት የቃሉን እውነት እንድንመረምር አሳስባችኋለሁ፡፡
ሄርሜኑቲክስ ሶስት ሂደቶች ያሉት ሲሆን
ምልከታ
ትርጎማ
ትግበራ ናቸው
እነዚህ ሶስቱ ቅደም ተከተላቸው ካለመጠበቅ ለተሳሳተ መረዳት እና አመለካከት ይመራናል ለምሳሌ ከ1 ቀጥታ 3 ላይ ዘለን ብንሄድ ጥቅም የለሽ እና ስህተተኛ የሆነ መረዳት ላይ ይተወናል፡፡
ሁለት አይነት አፈታት
1.ኤክስጄሲስ (Exegesis):- ይህ ከመ/ቅዱስ ውስጥ ወደ ውጪ ማንበብ/መተርጎም ነው፡፡ ምን ማለት ነው ቃሉ የሚናገረውን ትክክለኛ ትርጓሜ ማለት የፈለገውን ራሱን በራሱ እንዲፈታ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም “EXEGESIS is read out of the bible” ልንለው እንችላለን በዚህ መንገድ የመ/ቅዱስ ትክክለኛ ትምህርት ማግኘት ለእኛ የሚሆነውንም ትግበራ መረዳት እና በዛም እውነት መኖር እንድንችል የሚረዳን ትክክለኛ አፈታት ነው፡፡
2.ኤስጄሲስ (Eisegesis):- ይህ በሌላ ጎኑ ወደ መ/ቅዱስ ማንበብ የምንለው አፈታት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰዎች የራሳቸውን መረዳት እና ፍላጎት የሚደግፍላቸውን የቃሉን ጥቅሶች እየመዘዙ ሊተረጉሙት ይችለሉ፡፡ በዚህ አፈታት እውነቱን መፈለግ ሳይሆን እውነቱን ማረጋገጥ ብቻ ነው ለዚህም ነው “EISEGESIS IS READ INTO THE BIBLE” ልንለው እንችላለን፡፡ ኤክስጄሲስ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታ ይህ ቀላል ባለ መንገድ እኛ ልናደርገው የምችለው ነገር ግን ሰፋ ያለም እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ ጠለቅ አድርገን ኤክስጄሲስ እናድርግ ብንል ማህበረሰባዊ ዳራ፣ አርኪኦሎጂካል ዳራ፣ ስነልቦናዊ ቀረቤታ፣ የቃላት አፈታት ታሪካዊ ዳራ ሁሉ ልናካትትበት የምንችለው ሰፊ የአተረጓጎም ሂደት ነው፡፡
ቃል ክፍሉን መምረጥ በሙላት
ስነ-ፅሁፋዊ አውዱን መመርመር
ታሪካዊ-ባህላዊ አምዱን መረዳት
ትርጓሜውን መመስረት
ስነ-ጽሁፉ ውስጥ ያለውን ስነ መለኮታዊ መርህዎችን መረዳት እና መወሰን
ትግበራ ማካሄድ
በተላያዩ የመ/ቅዱስ ክፍሎች ላይ የተከሰቱ የአተረጓጎም ለውጦች
ይህን ክፍል ማካተት እንዴት በዘመናችን አንዳንድ አመለካከቶችቸ(አተረጓጎሞች) ከቀድሞዎቹ የቤ/ክ ሰዎች የተለየ እንደሆነ ካወቅን ልባችን የተከፈተ እንዲሆን ይረዳናል ተብሎ ከማሰበ ነው፡፡
1.የሴት ልጅ ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ
የቀድሞው ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መነሻ በማድረግ ሴት ልጅን ለወንድ ልጅ የበታች ተገዢ እንደሆነች ያስተምሩ የነበሩ የቤ/ክ አበዎች ነበሩ፡፡ ከሁሉ በላይ ለዚህ መነሻቸው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ሰፊውን ድርሻ የይዛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ካለ አተረጓጎም የተነሳ ለሴት ልጅ ይሰጥ የነበረው ቦታ የተዛባ እንዲሆን አድርጎ ነበር::
እነዚህን ጥቅሶች ይመልከቱ (1ቆሮ 11:7-9፣ 1ቆሮ 14:34-35፣ ቲቶ 2:3-5 ፣ 1 ጢሞ 2:12 ፣ ዘፀ 21:7፣ዘፀ20:17፣ ዘሌ 12:2-5፣ ዘሌ 27:3-7፣ ዘኁ 30:3-16፣ ዘዳ 21:10-14፣ ዘዳ 22:28-29፣ ዘዳ 25:11-12 ፣ዘሌ 20፡18፤ ፤ዘኁ 5፡13-31፤ዘዳ 22፡5፤ዘኁ 30፡3 16፤ዘሌ 12፡2-5፤ዘዳ22፡13-21 ወዘተ)
ይህ የህግ መጽሐፍ እንዲሁም ሌሎች የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ያላቸው አስተምህሮ አሉታዊ ምልከታ የሚፈጥሩ እንደሆኑ ስናነባቸው እንረዳለን ነገር ግን በዘመናችን ይህን ምልከታ ሆነ ትርጎማውን ያስቀጠለ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ የለም፡፡ ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ሥላሴ›› የሚለውን ቃል ጥቅም ላይ ያዋለው የቀደመው ዘመን የቤ/ክ አበው ተርቱሊያን የተባለ ጸሐፍ ስለሴት ሲናገር ‹‹እያንዳንዷ ሴት ሔዋን ናት ….አንቺ የገሃነም ደጅ ነሽ….አንቺ የተከለከለውን ዛፍ ቀዳሚ ቀማሽ ነሽ…እንቺ የመጀመሪያዋ መለኮታዊ ህግ አፍራሽ ነሽ….›› ሲል ለውድቀታችን ሙሉ ተጠያቂነት በሴት ላይ ያደርገዋል፡፡
ሌላው ከታወቁ ሰዎች መሃል ሚመደበው ማርቲን ሉተር ‹‹ሴት ልጅ ብትደክምና ልጅ በመውለድ ብትሞት ችግር የለውም ይህን ልታደርግ ነው በዚህ ያለችው›› ሲል የሴት ልጅ የመፈጠሯ ም/ክ ለመውለድ እንደሆነ ብቻ በመናገር አነስተኛ የሆነ አመለካከት አንፀባርቋል፡፡ ስለዚህ በዘመናችን የተከሰተው የአተረጓጎም እና የአፈታት ለውጦች ምክንያት የሆነው በሰው መሃል ያለው እውነትን ከመረዳት የሚጋርድ ሰዋዊ አወቃቀር መወገድ ነው፡፡
2. የባርያ ንግድ
መቼም መ/ቅዱስ የከፈተ ብሉይ ኪዳንን ያነበበ አንድ ነገር ማስተዋሉ አይቀርም የባርያ ንግድን ወይም ሰውን እንደ ባሪያ አድርጎ የመግዛት ባህልን ሲኮንነው ልክም አይደለም ሲል የምናገኘው አስተምህሮ የለም ነገር ግን ተግባራዊ ሆኖ ባለው የሰው ንግድ ላይ ተመስርቶ ሲናገር ትመለከታላችሁ፡፡ ለዚህም ደግሞ መተዳዳሪያ ህግ ሲሰጠው እናያለን፡፡
በዘመናችን ግን ሰውን ባሪያ አድርጎ በሰው ላይ ጌታ መሆንን የሚያስተምር ክርስቲያናዊ ዶግማ እንዳሌለ እናውቃለን ሁሉም የክርስትና ቅርንጫፎች በሙሉ በአንድነት የሚስማሙበት የባሪያ ንግድ ኢ-ሞራላዊ እንደሆነ ይስማማሉ ቃሉም ይህን ያስረዳል ታዲያ ይህ መረዳታችን መ/ቅዱስን ሻርን ያስብለናል በጭራሽ ልብ ልንል የሚገባው አንድ ነገር አለ የሚሰጠን አዲስ መጽሐፍ የለም ነገር ግን አዲስ መረዳት ቀድሞ ከነበረው አና በዘመናት ካረጀው መጽሐፍ እናገኛለን፡፡ ለዛም ነው አሁን የተባሉትን ጥቅሶች ተመልክተን ወደ ትግበራ የማንገባው በዘመን የተለያየን፣ በባህል፣ በአመለካከት ብስለት ተራቀን ፣ በማህበራዊ አደረጃጀታችን ልዩነት የለን እንደመሆናችን ትርጎማውን በጥልቀት ልናየው የሚገባን፡፡
ጥቅሶች፡- ዘፀ 21:2-21፣ ዘሌ 22:10-11 ፣ ዘሌ 25:44-46 ፣1ቆሮ 7:20-21፣ 1ቆሮ 12:13፣ ኤፌ 6:5-8 ፣ ቆላ 3:22 ፣ ቆላ 4:1፣ 1ጢሞ 6:1-2 ፣ ቲቶ 2:9-10 ፣ ፊሊ 1:15-16 ፣ ዕብ 2: 14-15 ፣ 1ጴጥ 2:18-20፣
ተፈጥሮ እና መጽሐፍ ቅዱስ
ስንቶቻችን ጋሊሊዮ ቴሌስኮፕ ከመስራቱ በፊት በርካታ ክርስቲያኖች ስለ ሶላር ሲስተማችን የሚያኑትን እናውቃለን ?
“ክዋክብት ፀሐይ እና ሌሎች የሰማይ ሰራዊት በሙሉ ምድርን ለማስጌጥ የተፈጠሩ በምድርም ዙሪያ የሚሽከረከሩ ምድር ግን የማትንቀሳቀስ ቀጥ ብላ በዛቢያዋ ላይ የምትኖር” እንደ ነበረች ነው
እስኪ በ21ኛው ክ/ዘመን እየኖረ ፀሐይ ምድርን ትዞራለች ብሎ የሚያስተምር የሚሰብክም ክርስቲያን አለ? በጭራሽ የለም! (በራሱዋ ዛቢያ ፕላኔቶቿን ይዛ በሚልክዌይ ጋላክሲ መካከል ያለውን ሳጊታሩየስ ኤ የተባለውን ብላክ ሆል የምታደርገው እሽክርክሪት እንዳለ ሳንረሳ ማለት ነው ይህም ቢሆን ፀሐይ ጭራሽ ምድርን ዞራ አታቅም) በእኛ እና በ16ኛው ክ/ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ያነበብነው ቃል እንድ አረዳዳችን ግን የተለያየ እንዴት ሊሆን ቻለ መልሱ አንድ ነው አዲስ መረጃ ስለ ተፈጥሮ ሲገለጥ ነገሮች ሚብራሩበት መንገድ መለወጡ የማይቀር ነው፡፡ እንደምናውቀው ቃሉ (መጽሐፉ) ሁሌ ልክ ነው የተሳሳተ ነገር ሊናገር እንደማችል ነው ስለዚህ በ16ኛው ዘመን የነበሩ አማኞች ክፍሎቹን የተረጎሙበት መንገድ ኤስጄሲካላዊ እንደሆነ መገመት አይከብደንም ወይም ከምልከታ ወደ ትግበራ እንደዘለሉ እንረዳለን፡፡
‹‹ፀሓይ ባለችበት ቆመች ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም……ፀሓይ በሰማዩ መካካል ቆመች…›› ኢያ10፡13
‹‹ዓለም እንዳትናወጥ ፀንታለች ማንም አይነቀንቃትም…››መዝ 93፡1
‹‹ፀሓይ ትወጣለች ትጠልቃችም ወደ ምትመጣበት ለመመስ ትጣደፋለች…›› መክ 1፡5
እንግዲህ ይህን ክፍል ያነበቡ የ16ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች ቃሉ የሚያስተምረን ፀሓይ እንደምትንቀሳቀስ ነው ብለው ነበር ለዚሀም ጋሊሊዮ ሀሰተኛ ነው በማለት ከሀገሩ እስኪባረር እና ህይወቱን በሙሉ የቤት እስረኛ ሆኖ እስኪቀር በተረዳው እውነት ተገፍቷል፡፡ ሁላችንም ልናስተውለው የሚገባው ባጠቃላይ 613 ገደማ የሚደርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተቀመጡ ትዕዛዛት አሉ በርካቶቹን ያልፈፀመ ሞት እንዲፈረድበት የሚያዙ ትዕዛዛት ነበሩ አሁን ላይ ማናችንም እንዚህን ህግጋት እንደ ወረዱ የማንተገብራቸው ተግባራዊነታቸው ለእኛ መሆን የማይችሉ ስለሆኑ በአዲስ ኪዳን መገለጥ የተነሳ ካገኘነው የጠለቀ እግዚአብሔራዊ መረዳት ነው፡
ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት እና መጽሐፍ-ቅዱስ
በዚህ ክፍል የምናያቸው የመ/ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ በማብራራት ሂደት አይደለም ም/ክ 7ቱ ጥቅሶች ሙሉ ለሙሉ ስር ነቀል የሆነ ገለጣ ለመስጠት እና መብራሪያ ትርጎማ ለማካሄድ ከዚህ ጠለቅ ያለ ሂደት መከተል ስላለብን ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ርዕስ ለማድረግ የምሞክረው ልባችንን ለአዲስ መረዳት እይታንም መክፈት እንድንችል መሰረት ለመጣል ነው የምሞክረው አዲስ ሰል ግን ከእኛ አረዳድ እንጂ ከቃሉ እውነት አንፃር እንዳልሆነ እንድትረዱ ፈልጋለው፡፡ አሁን እይታችን እንደ ቃሉ ሙላት እንጂ እንደ ጥቅሱ መቃኘት መተው አለብን አለበለዚያ የፀሓይ ዘዋሪነት የምድርን ቋሚነት በተረዱበት መንገድ መረዳታችን የማይቀር ነው፡፡ ጫካ ገብታችሁ ጫካውን ስለአንድ ዛፍ መጣመም ጫካው በጠማማ ዛፎች የተሞላ ነው ብለን እንደ ማንደመድመው ሁሉ በተወሰኑ ጥቅሶች የሙሉውን ቃል አስተምሮ አይደመደምም፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የተነገሩ ጥለቶች (Pattern) የሚጠቁሙ ጥቅሶች አሉ ልብ እንድትሉ እሻለው ስለ ተቃራኒ ፆታ አፍቃሪያን የተፃፉ አሉታዊ የታሪክ ጥለቶች እንዳሉ ነገር ግን እነዛ አግባብነት የጎደላቸው ተግባራት ግን ስለ ተቃራኒ ፆታ አፍቃሪነት ምንነት እና ልክነት መደምደሚያ ተደርጎ እንደማይወሰደው ሁሉ ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጥለት በተላበሱት ታሪኮች የተነገሩት አጠቃላይ መረዳት እንደማይሰጡ ልታሰምሩበት ይገባል፡፡ ነገር ግን አንድ አይነት እድምታ ለመፍጠር ከሞከርን አተረጓጎችን ኤስጄሲሳዊ እንደሚሆን መረዳት እና የተሳሳተ እንደሚሆን መገንዘብ አለብን፡፡
ጥቅሶቹም፡
ዘፍጥረት 19 ፡ 20-27
መሳፍንት 19፡22-27
ዘሌዋዊያን 18፡22
ዘሌዋዊያን 22፡13
1ቆሮ 6፡ 10
1ጢሞ 1፡10
ሮሜ 1፡24-27
1.ሰዶም እና ገሞራ (ዘፍ 19፡20-27) እንዲሁም የጊብዓ ሰዎች (መሳ 19፡22-27)
በመፅሐፍ ቅዱስ የሰዶምን ጩኸት የሰማው እግዚአብሔር መልአክ ወደ ሰዶሞ እንደላከ እንመለከታለን ይህ ጩኸት በከተማዋ ቅጥር ይደረግ የነበረ የግፍ መብዛት እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው። አንዳንድ አይሁዳውያን ፀሐፍት ከሚናገሩት የሰዶም ታሪክ አንዱ በከተማዋ ለማኝ ከመጣ እርዳታ ማድረግ ስለማይፈልጉ ግን አደረግን መባሉን ስለሚወዱ ስማቸው የተቀረፀበትን ሳንቲም ይሰጡት እና ይሸኙታል ከከተማው አንድም ሰው ግን ዳቦ ሆነ የሚጠጣ እንዳይሸጥለት ህግ ነበራቸው ሲሞት ይጠብቁና የሰጡትን ሳንቲን መልሰው ይወስዱ ነበር። አንዴ አንዲት ደግ ሴት ደብቃ ዳቦ ታቃብለው የነበረ ለማኝ ነበር እና እንዳልሞተ ሲያዩ ማን እንደሚመግበው አረጋግጠው ሴትየዋ ላይ ደረሱባት ከዛ ፊቷን ሙሉ ማር ቀብተው አደባባይ ሰቀሏት ንቦች እየበሏት በታላቅ ጩኸት ሞተች እንደ መምህራኑ ይህ ታላቅ ጩኸት አፋቸውን እንዲመረምር ፈጣሪን እንዳነሳሳው ይናገራሉ
ከዚ በተጨማሪ ሌላ ያላቸው አንድ ህግ ሰዶማዊ ያልሆነ የትኛውም ምፅአተኛን ያለመቀበል እና ያለማስተናገድ ህግ ነበራቸው። አስተውለን ከሆነ ሎጥ ሰዎቹ መልአክ መሆናቸውን ስላወቀ አልነበረም ግቡ ብሎ ችክ ያለው ይልቅ ከተማ አደባባይ ካደሩ የሚደርስባቸውን ግፉ ስላወቀ እንጂ እንዳለውም የበላይነታቸውን እና ገዢነታቸውን ለማሳየት ወደ ሎጥ ቤት የገቡትን ሰዎች ካላወጣህ ብለው አስጨነቁት የገዛ ደናግል ሴት ልጆቹን በተቃራኒው ሲሰጣቸው እንቢ ያሉት የወሲብ ጥማት ወይም ፍላጎት ስላልነበራቸው ነው ዋና ተግባራቸው በሌሎች ሰዎች ላይ የገዛ የራሳቸውን የበላይነት ማግነን ስለሚፈልጉ ነው።
በወንድ ላይ የበላይነትን ለመውሰድ ሌላ ወንድ ሲፈልግ በጥንት የነበሩ ሰዎች የሚያደርጉት ማኮላሸት ወይም የገዛ ሚስቱን እያየ መድፈር ወይም ራሳቸው ሰውየውን መድፈር ነው በሰዶም እየተከሰተ የነበረው ግፍ ይህ ነው ቅዱስ የሆነ የአንድነትን መንገድ ወደ ርካሽ ተግባር መለወጥ ነበር። ፍትሃዊነት የሌላቸው ለሰው ሰብዓዊ ክብር የማይሰሰጡ ከእኛ በላይ ማን አለ ባይነት
ሕዝቅኤል 16: 49-50 የሰዶምን ኃጢአት ግልፅ አድርጎ ይጠቅስልናል ፍቅር የሌለበት ስልጣኔ ፍቅር የሌለለበት የአመፃ አንድነት ነበራቸው ደም ለማፍሰስ የሚሮጡ እግሮች ነበሩ። ሰዶማዊነት እና የተመሳሳይ አፍቃሪነት አይመሳሰልም!
ገና ያላወቁትን ሰው እንደ ከተማ ሰዎች ተሰብስበን እንዋሰብ በማለት የተገለጠው የሰዶም ባህል ቅርንፋት በትክክል ጎልቶ የሚታይ ነው። ሰዶሞች ለወሲባዊ ህብረት የሰው ነፃ ፍቃድ እንግድነት የሚባል ነገር አይታወቃቸውም ነበር የሚታያቸው አንድ ነገር የራሳቸው ነገር ብቻ ነበር እንጃ የሆነ ብቻ የተበላሸ የሚለው ቃል የማይገልፀው ማህበረሰብ ሆነው ነበር።በሎጥ ቤት ባሉት ሰዎች ላይ የበላይነታቸውነ ለማሳየት የፈለጉት በመድፈር ነበር ይህ በእኛ ዘመን እስር ቤት አንዱ ሌላውን በመድፈር የበላይነቱን የሚያረጋግጥበት ክስተት አይነት ነው። ለሰውነተ ይህ #ውድቀት ነው
የሰዶም ኃጢአት የተበላሸ የወሲባዊ ዝንባሌ አልነበረም ይልቅ ፅንፍ የያዘ ልዩነትን ባለመቀበል የሚደረግ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ደፈራ እና ግንተላ ነበር። ሎጥ ቅዱስ ሰው ተብሎ የተጠቀሰበትን ጉዳይ ራሱ መጠየቅ አለብን ብዬ አስባለሁ የገዛ ልጆቹን ለመድፈር አሳልፎ የሰጠ ሰው ፃድቅ ነው ብለን የሞንቀበለው ወንድ ወንድን መድፈሩ ሴት በወንድ ከመደፈሯ ያንሳል የሚል ነው? የሰዶም ሰዎች ከላይ እንዳልኩት የሴክስ ፍላጎት አይደለም ያላቸው ይልቅ የሰውን ክብር ማንኳሰስ እና ማቆሸሽ እንጂ።
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ለእኔ ይህ(የሰዶም ተግባር) ነው የሚል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የለም።
ሰዶማዊያን በጣም ስግብግቦች እና ራስ ወዳድ ከመሆናቸው የተነሳ በጎ ማድረግን አጥብቀው የሚቃወሙ ህዝቦች ነበሩ። የዛሬ 2000ዓ.ዓ የነበረ በእሳት ዲን የጠፉ ከተሞች ለመሆን በቁ።ከዚህ ጋራ ተያይዞ ሰዶማዊ የሚለውን ቃል ከጥላቻ የተነሳ በአስረኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የመፅሐፍ ቅዱስ መምህራን ሰፍተውት አሁን ያለውን የዘፍጥረት 19 ታሪክ ሙሉ ለሙሉ የLGBTQIA+ ሰዎች ጋራ ለመለጠፍ መንገድ ፈጠረ ሲጀምር በአስረኛው ዘመን የነበሩ ሰዎች ስለ LGBTQIA+ ያላቸው ግንዛቤ ራሱ ከእውነት የራቀ ነው ለዘመናተ እንደ ሰዶም በእሳተ እንቃጠላለን ሰዶማዊያንን ካልገደልን የሚሉ አመለካከቶች ከዳር እስከ ዳር ተሰራጭቶ የኖረው እውነት ላይ በተመሰረተ እውነት አልነበረም ከንቱ የሰው ልጄ ድንቁርና እንጂ።
በሚገርም ሁኔታ ይህ ታሪክ የተመሳሳይ ፆታዊነት ሙሉ መጠሪያ ተደርጎ እስኪ ወሰድ የገነነ የመ/ቅዱስ ታሪክ ነው፡፡ ም/ክ ከባድ ሆነ የእ/ር ቁጣ የታየባቸው ስፍራዎች ስለሆኑ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን ጥፋት የሚያስከትል እንደሆነ ስሜቱ ባላቸውም ሰዎች ላይም ትልቅ ሽብር የሚፈጥር የሰው ፅንሰ-ሃሳብ የተመሰረተበት ኤስጄስስ አተረጓጎምን የተከተለ ሂደት ነው፡፡ አውነት ነው የሰዶም ሰዎች ከወንድ ጋር ፆታዊ ግንኙነት የሚያደርጉ እንደነበር መረዳት እንችላለን ነገር ግን የጥፋታቸው ሆነ የመደምሰሳቸው ም/ክ በእርግጥ ይህ ተግባራቸው ነው? የሰዶም ቅጣት አሰቃቂ ከመሆኑ የተነሳ ሰው ሙሉ እይታውን ስቶ በብዙሃኑ ግድብ ኤስጄሲሳዊ አተረጓም ላይ ታሪኩ ያላግባብ ለ2000 አመታት በስህተት ሲተረጎም ኖሯል አስተውላችሁ ከሆነ እ/ር የሰዶምን ኃጢአት አንስቶ በነቢያቱ በኩል ሲናገር ስለ ስለተመሳሳይ ፆታዊነት ጠቅሶ ግን አይደለም (አሞ 4፡ 1-11 ፣ ሰፎ 2፡ 8 11 ወዘተ)፡፡ አንዳንድ የመፅሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች በይሁዳ 1:7 የተጠቀሰውን "ሌላ ስጋን" የተከተሉት የሚለው አገላለፅ በሰዎች መካከል ስለሚደረግ ሩካቤ እንደማያወራ እና ሰው ካልሆነ ፍጥረት ጋራ የሚደረግን ሩካቤ የሚገልፅ እንደሆነ ያብራራሉ የሰዶም ታሪክም ሰዎቹ መልአክ በመሆናቸው ሌላ ስጋ የሚለውን ገለፃ የሚያሟሉ እንደሆኑ ይናገራሉ። በቀደመው አለም ከተለያዩ መንፈሳዊ አካላት ጋር የሚደረጉ ሩካቤ ስርአቶች እንደነበሩ ልንገነዘብ ይገባል ምንም እንኳ በሰዶም እና ጎሞራህ እና በዚሪያዋ ያሉ ሀገራት ይሃን ስለማድረጋቸው መረጃ ባይኖርም በርካታ ስነ መለኮት መምህራን (ተቃዋሚዎችም ብዙ እንደሆኑ እያሰብን) የሰዶም ኃጢአት ከፆታዊ ይልቅ ይበልጥ ማህበራዊ እና የሞራል እንደነበር ያትታሉ።
ባጠቃላይ ዘፍ19 ሆነ መሳ 19 ወስደን ፍቅር ስለሰፈነበት የተመሳሳይ ፆታዊነት ህብረት ወደምደሚያ ማስመር ሆን ብሎ ጭፍን መሆን እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ እንደሱ ካልን ግን በመ/ቅዱስ ያሉ አሉታዊ ታሪኮች አሉ በተቃራኒ ፆታዊያን የተከሰተ ስለዚህ እሱም ስህተት እና ኃጢአት ነው ብለን ልንደመድም ያስፈልገናል፡፡ የሰዶም ኃጢአት እንደሚከተለው ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ከታች ቀርቧል በእነዚህ ክፍሎች አጠቃላይ መረዳት የሰዶም ኃጢአት ስለ ፍቅር እንዳልነበረ ለመረዳት እንገደዳን የነበራቸው ፍትወታዊ ኃጢአትም የወንበዴዎች አስገድዶ መድፈር አንደነበር መገንዘብ ያስፈልጋል::
በጊብዓ የነበረው ታሪክም ከዚህ የተለየ እንዳልሆን እንገነዘባለን ወንድ ከወንድ ጋር ስለመገናኘት አልነበረም የታሪኩ ዋና ጭብጥ ምክንያቱም በሌዋዊው ፈንታ የሌዊውን እቁባት ፍትወታቸውን ለማብረድ ከመድፈረር አልታቀቡም ነበር ታሪኩ የሌላን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ፍጡርን ክብር ስለማርከስ እና ማንነቱን ስለመጣስ ነው፡፡ አብዝተን ይህን ክፍል (መሳፍንት 19) የማንሰማው ለጭፍን ጥላቻ ግብዓት ሆኖ ማገልገል የማይችል ስለሆነ ነው፡፡
የሰዶም ኃጢአቶች
አጠቃላይ ክፋት : ዘፍ 13፡13
ግፍኝነት እና የተጨቆኑትን አለማዳን ፡ ኢሳ 1፡ 10-17
የወንበዴዎች አስገድዶ መድፈር ፡ ዘፍ 19
ዝሙት እና ውሸተኝነት ፡ ት.ኤር 2፡14
ትዕቢትና ስግብግብነት፡ ሕዝ 16፡ 49፡50
እንግዳ ተቀባይ አለመሆን፡ ዘፍ 19
ድሆችን ማስጨነቅ፣ ጉራ፣ ትዕቢት፣ ጣዖት አምልኮ ፡ ሰፎ 2፡8-11
ማጠቃለያ
በፍቅር ኑሩ!
በቀጣይ ዳሰሳችን ደግሞ የቀሩትን ጥቅሶች በተወሰነ መልኩ ለማየት እንሞክራለን እስከዛ ይህን የበለጠ ለማሰብ እና ይበልጥም ለመመርመር እንድንሞክር አብዝተን እንመክራን፡፡ ይህን በዚህ ክፍል የቃኘነውን ጥቅስ የበለጠ ግላዊ ጥናት በማድረግ የበለጠ አስተሳሰባችንን እናስፋ ስንጀምር እንዳስቀመጥነው ሁሉም የራሱን ‹‹ነው›› በገዛ ጥናቱ እንጂ ከሌሎች መቀበል እንደማይችል አምናለሁ ስለዚህ ይህ እንደ መንደርደሪያ እንደሚሆናችሁ ትልቅ ተስፋ አለኝ!
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” 1ዮሐንስ 4፡ 16
ሮቢን ኢዮአብ
2017 ዓ.ም